10/12/2024
ቡናን አዘውትሮ መጠጣት የአንድን ሰው ዕድሜ በአማካይ ወደ ሁለት ዓመት ሊያስረዝም እንደሚችል ከፖርቹጋል የተገኘው አዲስ ጥናት ጠቁሟል፡፡ የኮይምብራ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በ አራት የተለያዩ አህጉራት በሚገኙ ተሳታፊዎች ላይ 85 ጥናቶችን አካሂደው ሦስት ኩባያ ቡና በየቀኑ መጠጣት በአማካይ 1.84 ዓመት ዕድሜ እንደሚጨምር በጥናታቸው አመላክተዋል፡፡
ጥናቱ እንደሚያመላክተው ቡና በውስጡ እንደ ፖሊፌኖል ያሉ ባዮአክቲቭ ውህዶችን ስለያዘ ቡናን መጠጣት የልብና የደም ዝውውር በሽታ፣ ካንሰር፣ የስኳር በሽታ እና የአእምሮ መታወክ ያሉ ሥር የሰደዱ ህመሞችን የመከላከል አቅም እንዳለው ያሳያል፡፡ በተጨማሪም ቡና ሰዎች ረዘም ላለ ጊዜ እንዲኖሩ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ጤናማ ሕይወት እንዲመሩ ሊረዳቸው እንደሚችልም ጥናቱ እንደጠቆመ ዘ ላቲን ታይምስ ዘግቧል።
የተገኘው ውጤት ተስፋ ሰጪ ቢሆንም ቡና ለሁሉም ፈውስ እንዳልሆነ ተመራማሪዎቹ አስጠንቅቀዋል፡፡ በተጨማሪም ጤናማ የአመጋገብ ስርዓት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴና ጄኔቲክስ የመሳሰሉት የአኗኗር ዘይቤዎችን መጠቀም ሰዎች ረጅም ዕድሜ እንዲኖራቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ተብሏል። አዋቂዎች በቀን ከሦስት እስከ አምስት ኩባያ ያህል መጠጣት እንደሚችሉ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ምንጭ፡- The Latin Times